በብኤኮ (METEC) ሃላፊዎችና ሰራተኞች ላይ በሚዲያ (በመንግስትና ደጋፊዎቹ) ከፍተኛ ቅስቀሳ የተመራ የCharacter Assassination ከተከናወነ በሗላ (ይህ ነገር ከእስሩ በኋላም ተባብሶ ቀጥሏል) ባለጊዜው መንግስት ሰዎቹን ለማስመሰል ከየተጠሩበት ስብሰባ በማፈስ ማእከላዊ ከከተታቸው ወደ 9 ወራት ተቆጥረዋል። የዋና ዳይሬክተሩ አያያዝና አመጣጥ ሁሉም ያየው ነው።
በመንግስት በተሰራጨው ፕሮፓጋንዳ ምክንያት ታሳሪዎቹ በየትኛውም ክስ ሳይከሰሱና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ከተጠርጣሪነት አልፈው ወንጀለኛ ተደርገው ተቆጥረዋል። የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህጉ መጀመርያ በሰጡት የፕሬስ መግለጫ ላይ ተከሳሾቹን በተመለከተ ብዙ ነገር ያሉ ቢሆንም ከዚህ ፅሁፍ ጋር በቀጥታ የሚገናኙ ነጥቦችን እናንሳ።
1. ተከሳሾቹ ከ37 ቢልዮን ብር በላይ የሆነ ሀብት በሙስናና በህገወጥ የግዢ ሂደት ማባከን
2. ተከሳሾቹ በቡድን በመደራጀት እርስ በርስ መጠቃቀም
ይህ ሁሉ ሲባልና ሲደረግ ከተለያዩ ወገኖች ‘ክሱ የፖለቲካ ይዘት ያለውና የአንድ ክልል/ብሄር ተወላጆችን ለማጥቃት የተወጠነ ይመስላል/ነው’ የሚል አስተያየትና ቅሬታ ሲቀርብ ቆይቷል። ከጠ/ሚሩ ጀምሮ ከፍተኛ የመንግስት ሰዎች ግን ይህን ቅሬታ በከፍተኛ ስሜት ሲያተባብሉ ቆይተዋል። እንግዲህ የሚከተሉትን ሀቆች አንብቡና የራሳችሁን ፍርድ ስጡ።
1. በመጀመርያው የክስ ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱት 35 ሰዎች 31 የትግራይ ተወላጆች ናቸው።
2. በኣሁኑ ወቅት የተከሳሾቹ ቁጥር ወደ 58 ያደገ ሲሆን ከነሱም 45ቱ አሁንም ከትግራይ ናቸው።
3. አቃቤ ህጉ በሁሉም ክሶች/ተከሳሾች ላይ ከበቂ በላይ የሰነድ ማስረጃዎች አሉኝ ቢልም በየችሎቱ የታየው እውነታ ግን ተቃራኒው ነው። በአብዛኞቹ ክሶች ላይ የተከሳሾችን ተጠያቂነት የሚያሳይም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚያመላክት የሰነድ ማስረጃ ማቅረብ አልቻለም ያቀረባቸውም በአመዛኙ ውድቅ ተደርገውበታል። ከነዚህ ክሶች መካከል መንግስትና ጠ. አቃቤ ህግ እጅግ የጮሁለትና በዶክመንተሪ መልክ ተላልፎ የብዙ የዋህ ወገኖችን አመለካከት ያዛባው የ’መርከብ ግዥ’ ጉዳይ አንዱ ነው።
4. ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት የተነሳ አቃቤ ህጉ ክሶቹን በሰው ምስክሮች ለማሰደገፍ ተገዷል። የቀረቡት ምስክሮች የተከሳሾቹ የስራ ባልደረቦች ናቸው ቢባልም ብዙዎቹ አለቆቻቸው የነበሩና ጉዳዩ የብሄርና የፖለቲካ ይዘት ባይኖረው ኖሮ ቀድመዉ ተጠርጣሪ የሚሆኑ ነበሩ። የተቀሩት እንኳን ምስክር ሊሆኑ ተከሳሾቹንም ሆነ ክሱ የሚያነሳውን ጉዳይ በፍጹም የማያውቁ ናቸው። በጣም የሚያስደምመው ነገር ግን ከምስክሮቹ ውስጥ አንድም የትግራይ ተወላጅ እንዳይኖር መደረጉ ነው።
5. ለነገሩ ሜቴክ ከሚሰሩት የትግራይ ተወላጅ ሲቪልም ይሁን ሚሊተሪ
ሰራተኞች ከሞላ ጎደል ሁሉም ዘብጥያ ወርደዋል የተረፉትም ተሳደው ወጥተዋል።
6. አቃቤ ህግ ያቀረባቸው ምስክሮችም ቢሆኑ ለህሊናቸውና ለእውነት ስለመሰከሩ የተከሳሽ ምስክሮች እስኪመስሉ ድረስ የራሱን የአቃቤ ህግ የክስ መሰረቶችን ንደዋቸዋል። ይህን ኪሳራ ለመቀነስ ሌሎች ምስክሮችን (በተለይም በጭፍን የብሄር ጥላቻ የተገፋፉ ወይም በሹመት ይገባን ነበር ስሜት ያኮረፉ) ለማቅረብ ሞክሯል። የእነሱም ምስክርነት ጥላቻቸውንና የቆየ ኩርፍያቸውን ከማሳየት የዘለለ የክሶቹን ጭብጥና የተከሳሾችን ጥፋተኝነት ማመላከት አልቻለም። አነዚህ ምስክሮች ከተከሳሾቹ ወይም ከጠበቆቻቸው ለተሰነዘሩባቸው እጅግ ቀላልና መሰረታዊ መስቀለኛ ጥያቄዎች መልስ መስጠት አለመቻላቸው አቃቤ ህጎችን ያሳቀቀ: ዳኞችን ያስገረመ: በየችሎቱ የነበሩትን ታዳሚዎች ያስደመመ ትዕይንት ነበር። ለዚህ አይነተኛ ማሳያ ኮሎኔል ጌቱ የተባለ የአቃቤ ህግ ምስክር ያሳየው አስደንጋጭ ነገር ነው።
7. ለማስታወስ ያህል ኮ/ል ጌቱ የተባለው ሰው ሜቴክን አስመልክቶ መንግስት ባቀነባበረው ፊልም ውስጥ በ’አስረጅነት’ የተሳተፈ ብቸኛ የተቋሙ የስራ ሃላፊ ነው። ይህ ሰው በራሱ አንደበት የ ‘መርከብ ግዢ ቡድን ሀላፊ’ ነበርኩ ቢልም እራሱን ተፈጽሟል ከሚለው ጥፋት ንጹህ አድርጎ ያቀርባል። በሱ ስር የነበሩትን በተለይም የትግራይ ተወላጅ ሰራተኞችን ግን ከተቋሙ የበላይ ሀላፊዎች ጋር በመመሳጠር ይከሳቸዋል። የፊልሙ ሰሪዎችም ግለሰቡን ጭራሽ እንደ ተቆርቋሪ ዜጋ አቅርበውታል። ከዛም አልፎ በአቃቤ ህግ ከተከፈቱት የክስ መዝገቦች ‘የመርከብ ግዥ’ ጉዳይ አንዱ ቢሆንም የቡድን መሪውን ኮ/ል ጌቱን ከመክሰስ ይልቅ የራሱ ምስክር አድርጎ ችሎት ላይ አቅርቦታል። እንግዲህ ‘ፍርድ ሂደቱ’ ጉድ ከመቼውም ጊዜ በላይ የተገለጠው ይሄኔ ነው። አቃቤ ህጉ ይህን ግለሰብ መልስም ጭምር እየነገረ ጠይቆ ከጨረሰ በኋላ ተከላካይ ጠበቆች መስቀለኛ ጥያቄ ማቅረብ ጀመሩ። ኮ/ል ጌቱ ለሚጠየቀው መስቀለኛ ጥያቄዎች ምንም አሳማኝ መልስ መስጠት ስላልቻለ አቃቤ ህጉ ዳኞች በግልጽ እስኪገስፁት ድረስ ‘ተቋውሞ!’ በሚል ጩኸት ችሎቱን በተደጋጋሚ ያውክ ነበር። ይህ ሁሉ ሆኖ መስቀለኛ ጥያቄዎችን እንዲመልስ በዳኞች የታዘዘው ኮ/ል ጌቱ ለመጨረሻው ጥያቄ የሰጠው አጭር መልስ በሜቴክም ይሁን በሌሎች ጉዳዮች ተከሰው በየእስር ቤቱ የሚታሹት የትግራይ ተወላጆች በባለጊዜዎች የተጠነሰሰ የማንነትና የፖለቲካ ጥቃት ኢላማ መሆናቸውን ቁልጭ አድርጎ ያሳየ ነበር። ምልልሱ የሚከተለውን ይመስል ነበር።
የተከ. ጠበቃ: እንግዲህ ዛሬ ለችሎቱ በሰጡት ምስክርነት የተከሳሽን ጥፋተኝነት የሚያሳይ አንዳችም ነገር አላነሱም። ስለዚህ በምን ላይ ተመስርተው ነው ተከሳሹ ላይ ለመመስከር የመጡት?
ኮ/ል ጌቱ: ያው ተከሳሹ ትግሬ ስለሆነ ከዘመዶቹ ጋር ተመሳጥሮ መዝረፉ አይቀርም ብየ ነው።
በዚህ ጊዜ ዳኞች የችሎቱን ስነ ስርአት ማስከበር ፍጹም እስኪያቅታቸው ድረስ የሁሉም ሰው ስሜት ክፉኛ የተነካ ሲሆን በተለይም የተከ. ጠበቃው የምስክሩ (ኮ/ል ጌቱ) አመለካከትና አገላለጽ እጅግ አጸያፊ ሲል ኮንኖታል። በሚገርም መልኩ ፍርድ ቤቱ ከምስክሩ እጅግ ዘረኛ መልስ ይልቅ የጠበቃውን ንግግር መገሰጽን መርጧል።
ከላይ ለመግለጽ ተሞከረው ህግን ሽፋን በማድረግ በተቋሙ ሰራተኞች በሆኑት የትግራይ ተወላጆች ላይ የተከፈተ የሚመስል ዘመቻ በሌሎች ተቋማትም እንደተፈፀመ የሚያመላክቱ በርካታ ማሳያዎች አሉ። ከዚህ ጋር በተገናኘ የተወሰኑ ትዝብቶችን እናስቀምጥ።
1. የተከሳሾቹ ዋና ሀጥያት ‘ትግሬነታቸው’ እንጂ በአቃቤ ህግ የተከሰሱበት ‘ጥፋት’ እንዳልሆነ የምታውቁት በየታሰሩበት ቦታ መለያቸው ‘ትግሬነታቸው’ ብቻ መሆኑን ስታዩ ነው።
2. ጠ/ሚሩ በቅርቡ አክሱምን በጎበኙበት ጊዜ ‘የትግራይ ተወላጆችን ብቻ ኢላማ አላረግንም’ ቢሉም በየቀኑ ወደ ቂሊንጦና ቃሊቲ ከሚጎርፈው የእስረኛ ጠያቂ ውስጥ ከግማሽ በላይ የትግርኛ ተናጋሪ መሆኑን ስታዩ እውነቱ የቱ እንደሆነ በደንብ ይገባችኋል።
3. የትግራይ ክልል መንግስት መሪዎች በቅርቡ ስለ ጉዳዩ የተወሰኑ ቅሬታዎችን ቢያሰሙም ከዚህ ያለፈ የተደራጀ ጥረት መደረጉን የሚያመላክት ነገር አይታይም። ለምሳሌ ከክልሉም ሆነ ከፌዴራል ባለስልጣናት (የህውሓት ውክልና ያላቸው) ታሳሪዎቹን (በተለይ ቂሊንጦ ያሉትን) መጥቶ የጠየቀም ይሁን በተዘዋዋሪ ለመገናኘት የሞከረ አንድም ሰው/አካል እስካሁን አለመኖሩ በጣም ያስገርማል ያሳዝናልም።
4. በርካታ ታሳሪዎች የቆየና አዲስ አካላዊ ወይም ስነ ልቦናዊ የጤና ችግሮች ተጠቂ እየሆኑ ቢሆንም አስፈላጊውን ህክምናና ድጋፍ እያገኙ ግን አይደለም።
5. በጣም አሳሳቢው ጉዳይ ግን የታሳሪዎቹ ቤተሰቦች እየደረሰባቸው ያለው ኢኮኖሚያዊና ስነ ልቦናዊ ጫና ነው። ለምሳሌ ከታሰሩት ተጋሩ የሜቴክ ሰራተኞች ውስጥ ሁሉም ማለት ይቻላል የሚሊተሪ አባላት ናቸው። በሚሊተሪዉ አሰራር ደግሞ አንድ አባል በስራ መደቡ ከ6 ወር በላይ ካልተገኘ ደሞዙ ሙሉ በሙሉ ይቋረጣል። የአብዛኞቹ ቤተሰብ ደግሞ ሌላ መተዳደርያ ገቢ የለውም። ይህ ማለት እንኳንስ ለነሱ ስንቅ ሊቋጥር ለራሱም መሆን ስለማይችል (ቀለብ፣ ኪራይ፣ የልጆች የት/ት ክፍያ) ቤተሰብ በቅርቡ የመበተን አደጋ ተጋርጦበታል።
6. እንግዲህ እስካሁን በአጭሩ የተገለፁትንና በትግራይ ተወላጅ የሜቴክም ሆነ ሌሎች ሰራተኞች ላይ የደረሱት ፈርጀ ብዙ ጥቃቶችና ችግሮች እንዲሁም ቀጣይ ፈተናዎች ለመፍታት የተቀናጀ ጥረትና ስራ ይጠይቃል።
ለጊዜው የሚከተሉት ጉዳዮች ላይ ቢተኮር ይመረጣል።
ሀ. የትግራይ ክልል/ህወሓት/ ነገርየው የፖለቲካና የብሄር ጥቃት ነው ካለ ቢያንስ ታሳሪዎችን መጠየቅና ማበረታታት ቤተሰቦቻቸውንም መደገፍ አለበት። የትግራይ ህዝብን አደራጅቶም ታሳሪዎቹ ፍትህ እንዲያገኙ መታገል አለበት።
ለ. የአብዛኞቹ ታሳሪዎች ጉዳይ በፍርድ ቤት ምስክሮች እየተሰሙባቸው ስለሆነ በችሎቶቹ በመገኘት ሂደቱን መከታተልና በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች የተቀናጀ ዘመቻና ቅስቀሳ መደረግ አለበት። በተለይም ተጋሩና ሌሎች ፍትህ ፈላጊ ብሎገሮችና አክቲቪስቶች ትልቅ ሀላፊነት አለባችሁ።
ሐ. የታሳሪዎች ቤተሰቦችን ለመደገፍና ከመበተን ለመታደግ ተጋሩ ባለሃብቶችና ተቋማት ከወዲሁ መንቀሳቀስ አለባቸው።
መ. ማንኛውም ፍትህ ወዳድ ዜጋ በተለይም የሃይማኖት አባቶች፣ አርቲስቶች፣ ወዘተ የነዚህን ወገኖች መንፈስ ለማጠንከር መስራት ይገባቸዋል።
By Abraham Asefa