Ethiopia: Electric Power Administration to be at the hands of Kilils

አዲስ አበባ ፣ ህዳር 17፣ 2008 (ኤፍ.ቢ.ሲ) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በክልሎች ስር እንዲተዳደር እየተሰራ መሆኑ ተነገረ።

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገብረእግዚአብሔር ታፈረ፥ ለሕብረተሰቡ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል አደረጃጀት ለመፍጠር ታልሞ ነው ድጅቱ በክልሎች ስር እንዲተዳደር የሚደረገው ብለዋል።

ምንም እንኳን ሥራው ገና የተጠናቀቀ ባይሆንም በዋና ዋና ከተሞች ተግባራዊ ለማድረግ የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን አቶ ገብረእግዚአብሔር ተናግረዋል።

አገልግሎቱን የሚጀምሩ እንደመኖራቸው ሁሉ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ስር ሆነው የሚቆዩም መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ ከባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት፥ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታየውን የኃይል መቆራረጥ በዘላቂነት ለመፍታት እንዲቻል የኤሌክትሪክ አገልግሎትን በክልሎች ስር የማስተዳደር ሥራ እንደሚጀመር  መናገራቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፥ ችግሩን ለመቅረፍ የቆዩትን የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ደረጃ በደረጃ ለመቀየር ሥራ ተጀምሯል።

በዚህ ዓመት ዝግጅቱ ተጠናቅቆ በቀጣዩ ዓመት ወደ ተግባር የሚገባ አዲስ አሰራር መኖሩን ጠቁመው፥ የፌዴራል መንግሥት በሁሉም ቦታ ተበትኖ ማስተዳደር ያቃተውን ድርጅት ክልሎች በየክልሉ እንዲረከቡ የማድረግ ሥራ ተጀምሯል ብለዋል።

ይሄም ለአስተዳደር ስለሚያመችና በዚያው ልክ ተጠያቂነትን የሚያሰፍን በመሆኑ ለመተግበር የአደረጃጀት ጥናት ተካሂዶ አልቋል።

በቀጣይ ከኃይል አቅርቦት አኳያ ምንም የሚያሰጋ ነገር የለም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ግልገል ጊቤ ሦስት ተጠናቅቆ አሁን ካለው የኃይል አቅርቦት በእጥፍ የሚያሳድግ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችለውን ሥራ በከፊል መጀመሩን ጠቁመዋል።

ምንጭ፦ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት

የተጫነው፦ በሙለታ መንገሻ

Leave a Reply