ከአማራ ክልል መንግስት የተሰጠ የአቋም መግለጫ

ሰላም የዘላቂ ልማታችን ዋስትና ነው!
የአገራችን ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መልከ ብዙ የሆነ እና አስደማሚ ታሪክ፣ ባህል፣ ወግ እና አኗኗር ያላቸው ህዝቦች ናቸው፡፡

እነዚህ ህዝቦች የማይነጣጠሉ መሆናቸውና ምንጫቸውም ከልዩነታቸው ይልቅ በእድሜ ጠገቡ አንድነታቸው እርስ በርሱ ተገምዶ የተፈተለና የማይነጣጠል ነው፡፡ የዚህ ማሳያው በሁሉም የአገራችን ክፍሎች ያሉት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በአብሮነት፣ በመተሳሰብና በፍቅር ተዋህደው የኖሩ፣ እየኖሩ ያሉና የሚኖሩ በመሆናቸው ነው፡፡ ይህንን ዴሞክራሲያዊ አንድነታቸውን ለማጠናከር ሰፊ ስራ የሚጠይቀን በመሆኑ ይህንኑ የማድረግ ስራ አንዱ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አካል ተደርጎ ሲሰራ ቆይቷል፡፡

ከዚሁ ትይዩ ልማትን ለማረጋገጥና መልካም አስተዳደርን ለማስፈን እንዲሁም የህዝብን ጥያቄ ለመመለስ ሰፊ ርብርብ ሲደረግ ቆይቷል፤ በመሆኑም በሀገራችን ባለፉት ሁለት አስርት አመታት የሀገራችንንም ሆነ የክልላችን ተስፋ ያለመለሙ አንጸባራቂ ለውጦችና ስኬቶች በሁሉም ዘርፍ ተመዝግበዋል፤ ምንም እንኳ በዚህ ለውጥ ምልአተ ህዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ ባይቻልም ተስፋ ሰጭ ጅምር ነው፡፡

ይሁን እንጂ ስር ሰዶ ከቆየው ህዝብን በተሟላና ቁርጠኛ በሆነ የአመራር ብቃት የመምራት አቅም ማነስ እና በአፈጻጸም ከሚታዩ ጉድለቶች የተነሳ የህዝብ እርካታ በሚፈለገው ልክ ያለማረጋገጥ ጉድለቶች እየተፈታተኑን ይገኛሉ፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክልላችን አንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱት ግጭቶችና የሰላም እጦቶች በማሳያነት ይጠቀሳሉ፡፡
በክልላችን በርካታ አካባቢዎች ሰላማዊው የልማትና የዕድገት ጥረት እንቅስቃሴዎች ያለ አንዳች መሰናክል እየተከናወኑና ፀረ-ድህነት ትግሉ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ በተለይም ደግሞ በወቅታዊው የተቀናጀ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃ ስራ አርሶ አደሩና መላ ቤተሰቡ በጋለ የንቅናቄ መንፈስ በመፈፀም ላይ ይገኛሉ፡፡

ይሁን እንጂ በክልሉ የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ወልዲያ ከተማ ህዳር 24 ቀን 2010 ዓ.ም በወልዲያ ከነማ እና በመቀሌ ከነማ የእግር ኳስ ክለቦች መካከል በወልዲያ ሊካሄድ በነበረው ውድድር ላይ በደጋፊዎች መካከል ከጨዋታው ቀድሞ በተነሳ ግጭት የሰው ህይወት ማለፉንና ንብረት መውደሙን ተከትሎ በቅርቡ የጥምቀት በዓል በተከበረ ማግስት የቃና ዘ-ገሊላ ዕለት ጥር 12 ቀን 2010 ዓ.ም የሚካኤል ታቦት ወደ መንበሩ እየገባ ባለበት ወቅት በወጣቶችና በፀጥታ አካላት መካከል በተቀሰቀሰ ግጭት በድጋሚ የሰው ህይወት ህልፈት፤ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመት ደርሷል፡፡ ውሎ ሲያድርም ግጭቱ በቆቦ እና መርሳ ከተሞች የቀጠለ በመሆኑ የዜጎች ህይወት አልፏል፤ የአካል ጉዳትና የንብረት ውድመትም ተደማሪ ችግሮች ናቸው፡፡ በዚህ ሁሉ ጥፋት በምንም የማይተካው የሰው ህይወት በማለፉ እና አካል በመጉደሉ እንዲሁም ንብረት በመውደሙ የክልሉ መንግስት ጥልቅ ሀዘን የተሰማው መሆኑን ገልጿል፡፡

ግጭቶቹ መነሻቸው መሰረታዊ የሆኑ የህብረተሰቡ ዴሞክራሲያዊና ህገ-መንግስታዊ ጥያቄዎችና ልዩ ልዩ ቅሬታዎች ሲሆኑ እነዚህንም ቅሬታዎችና ጥያቄዎች ዴሞክራሲያዊና ህገ-መንግስታዊ በሆነ መንገድ ደረጃ በደረጃ ለመመለስ ጥረት እየተደረገና በትኩረት እየተሰራ ቢሆንም የሚከሰቱት ግጭቶች በተለያዩ ወቅታዊ መነሻዎች አላስፈላጊ ዋጋ እያስከፈሉ ያሉ መሆኑ በአሳዛኝነቱና በጐጂነቱ የሚታይ ነው፡፡

በዚህ ክስተት ከጉዳት ውጪ የሚገኝ አንዳችም ትርፍ ካለመኖሩም በላይ አንዳንዶቹ የግጭት አዝማሚያዎች ማንነትን እየለዩ ጥቃት የሚሰነዘርባቸው መሆናቸውና ዜጐች ለዘመናት ያፈሩት ሀብትና ንብረት በአጭር ጊዜ መውደሙ በምንም መንገድ የክልሉንም ሆነ ችግሩ የተከሰተባቸውን አካባቢ ህዝቦች የማይወክል ተግባር ነው፡፡ በዚህ ጥፋት ሰፋፊ የኢንቨስትመንት እርሻዎች፣ የግለሰቦች ሀብትና ንብረቶች፣ የመንግስት ተቋማት እና ተሽከርካሪዎች ውድመት ደርሶባቸዋል፡፡ እነዚህ የደረሱት ጉዳቶች ሁሉ በምንም መመዘኛ ሊፈጸሙና በዚህ ዘመን ሊታዩ የማይገቡ ተግባራት ናቸው፡፡ አመፁ የህግ የበላይነትን ከመጣሱ የተነሳ የዜጎችን የዕለት ተዕለት ህይወት በማናጋት ስጋት ውስጥ የጣለ እንዲሁም ለዘረፋም የዳረገና መንገድ በመዝጋት ጭምር የግንኙነት መስመሮችን የዘጋ ድርጊት ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ለዘመናት ማንነት ሳይለየው ተሳስሮ የኖረውን ህዝብ ለማቃቃር የተሞከረበት ነበር፡፡

እነዚህ አጠቃላይ ሁኔታዎች ግጭቱ የተከሰተባቸውን አካባቢዎችም ይሁን የመላው የአማራ ክልል ህዝቦች የማይገልጹ ሲሆን የአማራ ክልል ህዝቦች ከሁሉም ብሄር፣ ብሄረሰቦች እና ህዝቦች ጋር በፍቅር አብሮ የመኖር አኩሪ ባህልና ጥብቅ ህዝባዊ ትስስር ያላቸው በመሆኑ እነዚህና እነዚህን መሰል እንቅስቀሴዎች በእጅጉ ያወግዟቸዋል፡፡
ግጭቶቹ ከተከሰቱ በኋላም በአካባቢው የህግ ጥሰትና ስርዓት አልበኝነት በመንገሱ ዜጎች ሀብት ንብረታቸው እየተዘረፈ በመሆኑ በየደረጃው ውይይት በተደረገበት ወቅት ህዝቡ ሰላሙ እንዲጠበቅና መንግስት ፈጥኖ ህግ እንዲያስከብርለት እየጠየቀ ይገኛል፡፡

በመሆኑም መንግስት የዜጎችን ደህንነት የመጠበቅ ግዴታና ሃላፊነት ስላለበት ህግ የማስከበር ስራውን አጠናክሮ ማስፈፀሙን ቀጥሏል፡፡ በዚህም መሰረት ክቡር የሆነውን የሰው ህይወት በማጥፋት፣ አካ በማጉደል እንዲሁም ንብረት በማውደም የተጠረጠሩትን ግለሰቦች ቁጥጥር ስር ማዋል ተጀምሯል፤ በእነዚህ አካላት ላይ የተገኘው መረጃ ተጣርቶ እንደየጥፋታቸው መጠን ብይን የሚሰጣቸው ይሆናል፡፡

መንግስት የሰው ህይወት ያጠፉ፣ አካል ያጎደሉ እና ሃብት፣ ንብረት ያወደሙ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል በሚደረግ ጥረት ህብረተሰቡ መረጃ በመስጠትና ህገ-ወጦችን በማጋለጥ እያደረገ ላለው ትብብር የክልሉ መንግስት ምስጋና እያቀረበ በቀጣይም ይኸው የጋራ ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከዚሁ ጐን ለጐን ህብረተሰቡ በራሱ አደረጃጀት የአካባቢውን ሰላም እንዲያስጠብቅ በድጋሚ ጥሪ እያቀረበ ህገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን በብቃት በመመከት የህግ የበላይነትን በማስከበር የክልሉ መንግስት ሙሉ ሃላፊነቱን የሚወጣ መሆኑን ያረጋግጣል፡፡

ሰላም ወዳዱ የክልላችን ህዝብም በየአካባቢው የልማት ስራው ሳይቋረጥ በአብሮነት መንፈስ የሰላም ባለቤትነት ተግባሩን ለአፍታም ቢሆን ሳይዘነጋ ከፀጥታ ሃይሉ ጐን በመቆም ሰላም ለማረጋገጥ እና የህግ የበላይነትን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል፡፡
ሰላም የዘላቂ ልማታችን ዋስትና ነው!

Leave a Reply