አዲስ የመንግሥት አደረጃጀት እንደሚፈጠር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አስታወቁ

Addis Ababa, August 31, 2016:

ኢህአዴግ ሰፊ ተሃድሶ ለማካሄድ በወሰነው መሰረት በመጪው ዓመት አዲስ የመንግሥት አደረጃጀት እንደሚፈጠር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ አስታወቁ። በአማራና በትግራይ ክልሎች ከድንበር ጋር ተያይዞ ለተነሳው ችግር የየክልሎቹ ከፍተኛ አመራሮች ተጠያቂ እንደሚሆኑም ተናግረዋል።

በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ትናንት ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ እንዳስታወቁት፤ በሥራ አስፈጻሚና በምክር ቤት ደረጃ ያሉ የኢህአዴግ አመራሮች «ከእኔ በላይ ህዝብና አገር» የሚለው የቀደመው የድርጅቱ ባህል ይመጣ ዘንድ አዲስ የመንግሥት አደረጃጀት ተፈጥሮ በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ፓርላማው ሥራውን ሲጀምር እንዲቀርብለት በሙሉ ስምምነት ወስነዋል።

«የመንግሥት ሥልጣን የግል ኑሮ ማጎልበቻ አድርገን መመልከቱን ትተን እራሳችንን ለህብረተሰባችን ፈጣን ለውጥ መስጠት አለብን ብለናል» ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ማንኛውም አመራር የትም ቦታ ቢመደብ መሥራት እንዳለበትና ሥልጣንን ከቆዳው ጋር ማያያዝ እንደሌለበት መግባባት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል።

በአዲሱ የመንግሥት አደረጃጀት መሰረትም የኢህአዴግ አባላት ብቻ ሳይሆኑ ለእዚህ ሥርዓት ውጤታማነት ሊሠሩ የሚችሉና የተቀመጡ ፖሊሲዎችን የሚያስፈጽሙ አባል ያልሆኑ ግለሰቦችም ለህዝቡ ሲባል በመንግሥት ሥልጣን ውስጥ ሊካተቱ እንደሚችሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያም፤ ፀረ ዴሞክራሲ አካሄድ እንዳይኖር፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስፈጻሚውን አብጠርጥሮ መፈተሽና እርምጃ ማስወሰድ እንዳለበት፥ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የእንባ ጠባቂ ተቋማት እንዲጠናከሩ፥ የዋናው ኦዲተር መሥሪያ ቤት እንዲጎለብት ፍላጎቱና ቁርጠኝነቱ በመንግሥትና በድርጅቱ ዘንድ አለ። ከዚህ አንጻር በተለይ የፀረ ሙስና ትግሉ ሊጠናከር እንደሚገባና ሁሉም አስፈጻሚ እንቅፋት መሆን እንደሌለበት፣ እንቅፋት የሚሆን ካለም ከመስመር መውጣት አለበት ተብሎ ተወስኗል።

በተያያዘም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራና በትግራይ ክልሎች ድንበር አካባቢ(ጠገዴና ፀገዴ ወረዳዎች) ያሉ የወሰን ችግሮች እንዲፈቱ ህዝቡ ጥያቄ ካቀረቡ በርካታ ዓመታት ቢቆጠርም የየክልሎቹ አመራሮች ፈጣን ምላሽ ሊሰጡ አልቻሉም። በመሆኑም አሁን ለተፈጠረው ግጭት ተጠያቂዎቹ የየክልሎቹ ርዕሰ መስተዳድሮችና በየደረጃው ያሉ አመራሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

«ችግሩን ለሁለቱ ክልል ህዝቦች ብንተወው ኖሮ በራሳቸው ጥበብ ይፈቱት ነበር። የእዚህ ችግር ዋናው ባለቤትና እንዲወሳሰብ ያደረጉት የሁለቱ ክልል ከፍተኛ አመራሮች ናቸው። ስለዚህ ተጠያቂዎቹ እነሱ ናቸው» ያሉት አቶ ኃይለማርያም፤ የሁለቱም ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች ችግሩ የእኛ ነው ብለው እንደተቀበሉና ይሄም የመፍትሔው ግማሽ መሆኑን ነው ያስታወቁት።

የድንበር ጉዳይ በቀላሉ ሊፈታ የሚችልና ከዚህ በፊትም በህገ መንግሥቱ መሰረት ደቡብም ይሁን በኦሮሚያና አሁን ጥያቄ በተነሳባቸው በራሳቸው የአማራና ትግራይ ክልሎች ሳይቀር በቀላሉ መልስ የተሰጠው ጉዳይ ሆኖ ሳለ አመራሩ ህዝቡን ሳይሆን ቁራጭ መሬት በጭንቅላቱ ይዞ ስለሚከራከር ችግሩ ሊፈጠር መቻሉንም ነው አቶ ኃይለማርያም ያሰመሩበት። «አመራሩ ህዝቡን ማዕከል ቢያደርግ ኖሮ ይሄ ሁሉ ባልሆነ፤ አሁን ግን ህዝቡን ታሳቢ አድርጎ ለመሄድ አመራሮቹ ተስማምተዋል» ሲሉም ነው ያከሉት።

የተፈጠሩት ግጭቶች ለህዝቡ ጥያቄ ፈጣን ምላሽ አለመስጠት ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል ትልቅ ትምህርት የሰጠ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ህዝቡ ላሳየው ትዕግስት ምስጋናቸውን አቅርበው፣ የትግራይና የአማራ ህዝቦች በማይበጠስ ጠንካራ ገመድ የተሳሳሩና ማንም የማይለያቸው መሆናቸውን ነው የጠቆሙት።

በሌላ በኩልም የአገሪቷን እድገትና ሰላም ለማስቀጠል ሲባል የህግ የበላይነት መከበር ያለበት መሆኑና ለድርድርም የሚቀርብ ጉዳይ እንዳልሆነ በመጥቀስ ህዝቡም ይሄንን ጉዳይ በአፅንኦት እንዲመለከተው ያሳሰቡት አቶ ኃይለማርያም፤ ዴሞክራሲ ያለ የህግ የበላይነት ሊረጋገጥ ስለማይችል መንግሥት ሁሉንም አቅሙን አሟጥጦ እንደሚጠቀምና እርሳቸው ለሁሉም የፀጥታ ኃይሎች ይሄንኑ በተመለከተ ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን አስታውቀዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያም፤ የህዝቦች የማንነት ጥያቄ ክልሎች ሲዋቀሩ በህገ መንግስቱ መሰረት መልስ ተሰጥቶታል። በዚህ መሰረት ወልቃይትም በወቅቱ በትግራይ ክልል ውስጥ ሆኖ ተከልሏል። እስካሁን ድረስም ይሄንን በመቃወም በተቀመጠው ህገ መንግስታዊ አሰራር መሰረት ለክልሉ መንግስት የቀረበ ጥያቄ የለም። ይሁንና አሁንም ጥያቄ አለኝ የሚል አካል ካለ ክልሉ መልስ ለመስጠት ቁርጠኛነቱን ገልጿል። ክልሉ መልስ መስጠት ካልቻለም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፋጣኝ መልስ ይሰጣል።

አርአያ ጌታቸው

Source: Addis Zemen

 

Leave a Reply