በድርቅ የከሰመው ምርታማነት ስጋት ፈጥሯል

ዜና ሐተታ

ጌትነት ምህረቴ
አምና ምርት የታፈሰበት የራያ አላማጣ ሰፊ መሬት ዛሬ ሰብል እርቦታል ።ያ ለም መሬት በውሃ ጥም ተሰነጣጥቋል። አልፎ አልፎ የማሽላ ሰብል ቢታይበትም ፍሬ ሳይሰጥ መክኖ ቀርቷል። የአካባቢው ነዋሪዎችም ወደ ፊት እንስሳት በመኖ እጥረት እንዳያልቁ ስጋት ገብቷቸዋል።
በደቡብ ትግራይ ዞን በራያ አላማጣ ወረዳ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች በተጎበኘበት ወቅት በስር አሞራ ቀበሌ ያገኘናቸው የ60 ዓመቱ አርሶ አደር ወርቁ ገብረየስ ባላቸው ሁለት ሄክታር ማሳ በነሐሴ ወር 2007 ዓ.ም መጀመሪያ አካባቢ ሁለት ጊዜ ቢዘሩም በዝናብ እጥረት ቡቃያ እንኳ ሳያዩ ጠፍቷል። «ከወራት በፊት የተሻሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ብዘራም አብዛኛው በቡቃያ የተወሰነው ደግሞ በፍሬ ማውጫው ጊዜ ቀንጭሮ ምርት የመሰብሰብ ሀሳቤን መና አስቀርቶታል። እንደገናም ይህንኑ ማሳ ሽምብራ ብዘራበትም ምርት ሊሰጥ አልቻለም» ብለዋል።

አቶ ወርቁ በአካባቢው የሚኖሩ ሌሎች አርሶ አደሮችም ምርት ለማግኘት የነበራቸው ተስፋ በእንጭጩ እንደተቀጨ ይናገራሉ። ዛሬ በልበ ሙሉነት ይህን ያህል ምርት አገኛለሁ ለማለት አልታደሉም ይላሉ። ልጆቻቸውንና ራሳቸውን ምን መመገብ እንደሚችሉ በብርቱ ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን ይገልፃሉ።

«የዛሬን አያድርገውና አምና ይህንን ጊዜ ምርት በመሰብሰብ ሥራ ላይ እንጠመድ ነበር። ይህ ሁሉ መሬት ምርት የሚታፈስበት ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ልፋታችን መና ሆኖ ቀርቷል። ነገሩ ተስፋ ያስቆርጣል» ያሉት አርሶ አደር ወርቁ፣ በዚህ ሁኔታ አስር ቤተሰብ ማስተዳደር ከባድ ጭንቅ ውስጥ የሚከት እንደሆነ ነው የገለፁልን።
«በቤቴ ውስጥ የሚበላ እህል እየተሟጠጠ ነው። እህሉ ሲያልቅ ያሉኝን ሶስት ከብቶች ሽጬ ልጆቼን ለመመገብ እገደዳለሁ።ያ ሳይሆን የምግብ ዕርዳታ ቢሰጠኝ ጥሩ ነው» የሚሉት አርሶ አደሩ መንግሥት እስከ አሁን የምግብ እህል እርዳታ የባሰ ችግር ለአለባቸው ወገኖች መርዳቱን ይናገራሉ።
«የከብት መኖ መጥቷል ይባላል እኛ ግን አላገኘንም። እንዲሁም የውሃ ችግርም አጋጥሞናል። ብንጮህም ሰሚ አጣን። ለችግሩ መንግስት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት አለበት» በማለት ተናግረዋል።

12195005_563667943784558_6535395456461895695_o

12195077_563667983784554_3406090887125841771_o

ወይዘሮ ግምጃ መኮንን ስምንት ቤተሰቦቻቸውን በግብርና እንደሚያስተዳድሩ ይናገራሉ። «ሁለት ሄክታር መሬት ላይ ጤፍና ማሽላ ዘርተን ነበር። በዝናብ እጥረት ምርት የመሰብሰብ ሀሳባችን በአጭር ቀርቷል። ዓምና በዚህ ማሳ ላይ ከ30 እስክ40 ኩንታል ምርት ታፍሶበታል። ዘንድሮ ግን ምንም ማምረት አልቻልንም። ይኸው እጃችንን ወደ ሰማይ ዘርግተን ፈጣሪያችንን እየተማፀን ነው» ብለዋል። መንግስት ለእንስሳቱ የከብት መኖ ሰጥቶናል የሚሉት ወይዘሮ ግምጃ «ለእኛ ግን ምንም አልሰጠንም፤ ከምግብ እጥረቱ ጎን ለጎን የውሃ ችግር ህይወታችንን ከባድ አድርጎታል» ባይ ናቸው። ከብት ያለው ሰው ዕርዳታ አይሰጠውም ተብሎ አለመመዝገቡም ቅር እንዳሰኛቸው ገልፀዋል።
ሻምበል ዳኘው የ12ኛ ክፍል ተማሪ ነው። በአካባቢው ድርቅ በመከሰቱ እስካሁን በትምህርት ላይ ችግር እንዳልተፈጠረ የሚናገረው ሻምበል፤ ወደ ፊት በቂ ድጋፍ ካልተደረገ የምግብና የውሃ እጥረቱ ስለሚባባስ ትምህርት እስከማቋረጥ የምንገደድበት ሁኔታ ይፈጠራል የሚል ስጋት አለው።
አርሶ አደር አባተ አበራ በራያ አላማጣ ወረዳ ሀርሌ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ስድስት ጥማድ ማሳ ቢኖራቸውም በክረምቱ ወቅት ዝናብ ስላልዘነበ ምርት የማግኘት ምኞታቸው ተስፋ ቢስ መሆኑን ነው የተናገሩት። የማሽላ ማሳቸውም በቂ ዝናብ ባለማግኘቱ ፍሬ ስላልያዘ ለከብቶች መኖ ከመሆን ውጭ ምንም ሊፈይድ እንደማይችል ገልጸዋል።
ለከብቶች የሚሆን መኖ ስለሌለ ፍሬ ሳይሰጥ የቀጨጨውን የማሽላ ሰብል ከብቶቻችን እየመገብን ነው የሚሉት አርሶ አደር አባተ፣ይህ ሲያልቅ ግን በእንስሳቱ ላይ የሚጋጥመው ጉዳት የከፋ እንደሚሆን ነው የተናገሩት። በአሁኑ ጊዜም በአካባቢያቸው የከብት ዋጋ በጣም እንደቀነሰና በአንፃሩ የእህል ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ገልፀዋል። ለምሳሌም አንድ ጣሳ ማሽላ 6ብር የነበረ ሲሆን፤ ሰሞኑን ወደ 12 ብር ከፍ ብሏል ነው ያሉት።
የራያ አላማጣ ወረዳ 15 ቀበሌዎች አሉት የሚሉት የወረዳው አስተዳደር ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀራብሴ ከበደ በወረዳው አንደኛና ሁለተኛ ዙር የሰብል ግምገማ የተደረገ ቢሆንም ምርት ይገኛል ተብሎ አይጠበቅም።
ድርቁ ባስከተለው ጉዳት ለ15ሺ ተጎጂዎች ከመንግስት በተገኘ ድጋፍ እርዳታ ሲሰጥ መቆየቱን ገልፀዋል።በአሁኑ ወቅት የዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር በመጨመሩ ሲረዱ የነበሩትን ጨምሮ70ሺ ሰዎችን ለመርዳት ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። የእንስሳት መኖ ችግርን ለመፍታትም ከራያ ቢራ ጋር በመነጋገር ለአርሶ አደሩ የማከፋፋል ስራ እየተሰራ ነው። የውሃ ችግርን ለመፍታትም ቀደም ሲል ተቆፍረው ወደ ስራ ያልገቡትን በመንግስት ድጋፍ ቶሎ ወደ ስራ እንዲገቡ እንቅስቃሴ ተጀምሯል። ህዝቡ ከቀየው ሳይፈናቀል ዕርዳታ የሚያገኘበትን ስርዓት መንግስት እየተከተለ ነው ብለዋል።
እንደ አቶ ሀራብሴ ገለጻ በወረዳው32ሺ ሄክታር የሚለማ መሬት አለ። ባለፉት ሁለት ዓመታት ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተገኝቷል። አሁን ግን ምንም የሚሰበሰብ ምርት እንደማይኖር ተገምግሟል። ድርቁን ተከትሎ የበሽታ ወረርሽኝ እንዳይከሰትም ወረዳው በየቀኑ በጤና ባለሙያዎች አማካኝነት ጥብቅ ክትትል እያደረገ ነው።
በወረዳው 70ሺ ተረጂዎች ብቻ ናቸው ያሉት የሚል እምነት የለንም የሚሉት ኃላፊው ምክንያቱም በአሁኑ ጊዜ አስቸኳይ ዕርዳታ የሚስፈልጋቸው ተብለው የተለዩት ምንም እንስሳትና የእህል ክምችት የሌላቸው ናቸው። ሆኖም አሁን እንስሳትና የተወሰነ እህል ያላቸው ሰዎችም እህሉ ሲያልቅ እንዲሁም እንስሳቱም ሊሸጡ ስለሚችሉ በሁለተኛ ደረጃ መረዳት አለባቸው የሚል እምነት አለን ነው ያሉት። አጎራባች ወረዳዎችም ብዙም አጥጋቢ ምርት ያልተመረተባቸውና በድርቅ የተጎዱ በመሆናቸው ሁኔታውን አስቸጋሪ ያደርገዋል ብለዋል::

Source: Ethiopian Press Agency

 

Leave a Reply