በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከትግራይ ተወላጆች ማሕበር በሰሜን አሜሪካ የተሰጠ መግለጫ

በኢትዮጵያ በተለያዩ ዘመናት ወደ ስልጣን የመጡ ስርዓቶች የስልጣን ዘመናቸውን ለማደላደል እና ለማራዘም የተለያዩ በደሎች እና ግፎች በህዝብ ላይ ፈጽመዋል። ዳግማዊ አጼ ምንሊክ ሀገር ለማቅናት እና ለማስገበር በሚል በብሔሮች ላይ አለ የማይባል ግፍ ፈጽመው ራስ ገዝ የነበሩ ግዛቶችን በመውረር እና በመደምሰስ ሀገር መስርተዋል። እሳቸውን ተከትሎ የመጣው ተቀጥያ ዘውዳዊው የንጉስ ሃይለስላሴ አገዛዝም “ስዩመ እግዜብሔር” በሚል መጠሪያ ስልጣን ከህዝብ ድምጽ ሳይኾን ራሱን ከመለኮታዊ ሀይል የተሰጠው አድርጎ በመቁጠር ሀገርን እና ህዝብን በጭቆና ረግጦ ገዝቷል። የጃንሆይን ውድቀት ተከትሎ የተተካው ወታደራዊው የደርግ መንግስት በአፋኝነቱ ወደር የማይገኝለት አምባገነን ስርዓት በመትከል ሀገሪቷን የእልቂት አውድማ በማድረግ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በመማገድ የሚልዮኖች እልቂት በማስከተል ሀገር የደም ገንዳ እንድትኾን ፈርዷል። መጨረሻም በህዝቦች ትግል እና የማይተካ የህይወት መስዋእትነት ውርደቱን ተከናንቦ ወደ መቃብር ወርዷል። እነዚህ ሁሉ ስርዓቶች ለፈጸሙት ግፍ በኢትዮጵያ ታሪክ በብሔር ስም ተጠርተው ለፈጸሙት በደል “የእገሌ ቋንቋ ተናጋሪ” ሳይባሉ ተወቅሰዋል ተረግመዋል በህዝቦች ትግልም ተወግደዋል።

በ1983 ዓ/ም በህዝብ ልጆች መስዋዕትነት በተገኘ ድል ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ተተክሎ ዜጎች የመሰላቸውን የመናገር፣ የመጻፍ የመደራጀት፣ በማንነታቸው እና እምነታቸው ሳይሸማቀቁ የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው ለመወሰን የሚያስችላቸው ሕገ መንግስት አጽድቀው አዲስ የሀገር ግንባታ ምዕራፍ አብስረዋል። ይህንን ተከትሎም ኢትዮጵያ አለምን ያስደነቀ የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የዲፖሎማሲ ከፍታ፣ የተረጋጋ ሰላም ለሌሎች አፍሪካዊያን ጭምር ትሩፋት የሚሆን አቅም መገንባት ችላለች። በኢኮኖሚው እና ሌሎች ዘርፎች የተመዘገቡት አስገራሚ ለውጦች በዲሞክራሲ እና ሰብአዊ መብት አያያዝ ለማስፋት የህዝቦች የፍትሓዊ የልማት ጥያቄዎች፣ የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ እና የመልካም አስተዳደር እጦት ያንገሸገሸው ህዝብ በየአካባቢው በተለይም በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች ላለፉት አራት ዓመታት ድምጹን ሲያሰማ ቆይቶ ገዢው ግንባር ኢህአዴግ የህዝብን ድምጽ አድምጦ ምላሽ ለመስጠት በስር ነቀል ለውጥ ለማለፍ በወሰነው ውሳኔ መሰረት አዲስ አመራር እስከ መሰየም ድረሰ። ለዚህም አመራር ማሕበራችን ድጋፉን መስጠቱ ይታወሳል።

ይህ የህዝብና ጥያቄ እና ብሶት ይመልሳል የተባለው አመራር ግን እየዋለ እያደረ ህዝባዊነቱ እየተሸረሸረ የህዝብን ጥያቄ በተለይም የወጣቱን የስራ አጥነት ችግር እና ሁለንተናዊ ለውጥ ፈላጊነት መመለስ አቅቶት ሲንገዳገድ ተስተውሏል። ከዚህም ባለፈ ሀገር ወደ ማትወጣው ሁከት እና ብጥብጥ እንድታመራ የመሪነት ሚናውን መወጣት አቅቶት ዛሬ በኢትዮጵያ አስነዋሪ እና አጸያፊ ድርጊቶች ማለትም በመንጋ ፍትሕ ሰው በአደባባይ የሚሰቀልባት እና በድንጋይ ተቀጥቅጦ ወደ ሚገደልባት ስርዓት አልበኝነት የነገሰባት ሀገርነት (stateless) ተሸጋግራለች። ዜጎች በማንነታቸው ምክንያት በደረሰባቸው ጥቃት በመሸሽ ወደ ጎረቤት ሀገር የሚሰደዱባት ሀገር ተፈጥራለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሀገሪቱ አሁን የሚከስቱ እና ባለፉት ዓመታት የተከሰቱ ጉድለቶች ማለትም መሪው ድርጅት ኢህአዴግ እንደ ጉድለት ወስዶ ያመነባቸው እና በጋራ መፍትሔ ለመስጠት የተሰማማባቸው እንዲሁም አቅጣጫ ያስቀመጠላቸው የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ሙስና፣ የሕግ የበላይነት አለመከበር ጉዳዮች ዛሬ የአንድ ብሔር እና ድርጅት ችግሮች እንደኾኖ ተደርገው በመንግስት ሚዲያ በየቀኑ እየተሰበኩ ይገኛሉ። በፊት በውጭ ሀይሎች በሚዘወሩ የጥፋት ሀይሎች ይቀርቡ የነበሩ አንድን ህዝብ የሚወነጅሉ ክሶች ዛሬ መንግስት በሚያስተዳድራቸው የሚዲያ አውታሮች ከአሁን በፊት ተሰምቶ በማያቅ አስደንጋጭ አገላለጽ “ትግርኛ ተናጋሪ” በማለት አንድን ህዝብ ለእልቂት እና ጨፍጨፋ በሚያጋልጥ ልክ በ1994 እንደ ፈረንጆች አቆጣጠር በሩዋንዳ የተፈጸመው የጅምላ የዘር ማጥፋት ያስከተለውን የሬዲዮ ማይል ኮሊንስ ርዋንዳ ቅስቀሳ በሚስተካከል መልኩ ወደ ህዝብ ተሰራጭቷል።

በዚህ “የፍትሕ ሰቆቃ” በተሰኘ ዘጋቢ ፊልም፣ በመንግስት ቁጥጥር ስር ባሉ ሚድያዎች ሲሰራጭ ለተመለከተ ሰው ተፈጸሙ የተባሉት ግፎች አሳዛኝ ቢሆኑም ወደ አንድ ህዝብ ያነጣጠሩ አነጋገሮች፣ መንግስት በሽብር ወንጀል እና በወቅቱ ጠላት ተብሎ በተፈረጀ የጎረቤት ሀገር መንግስት ጋር በማበር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በተቃራኒ ቆመዋል በማለት ከሶ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው እና ጥፋተኛ ብሎ ወሳኔ ያሳለፈባቸው ሰዎች የሚሰጡት በጥላቻ የተነከረ ምስክርነት እጅጉን አስደንጋጭ ሆኖ አግኝተነዋል። የሚገርመው ነገር ደግሞ እነዚህ በቁጥጥር ስር ሲውሉ ሀገር ይመራ የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች እና አመራሮች አሁንም ስልጣን ላይ ያሉ ቢሆንም ዘጋቢ ፊልሙ እነሱን ወደ ጎን በመተው ህዝብን “ትግርኛ ተናጋሪ” በማለት ፈርጆ የስርዓቱን ሀጥያት ወደ አንድ ህዝብ ያጣበቀበት አኳሀን ጸረ ህዝብ ተግባር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

ይህ ከአንድ ሀገርን እመራለሁ ከሚል መንግስት የማይጠበቅ አሳፋሪ ድርጊት ማሕበራችን አጥብቆ ያወግዘዋል። ከዚያም በዘለለ ጉዳዩን እንደ ካሁን በፊት መሰል ተግባራቶች በአለም አቀፍ ሕግ እንዲታይ ጠንክሮ ይሰራል። መንግስት ይህ ድርጊት ጸረ ህዝብ መሆኑን ተረድቶ ለህዝብ እና ሀገር ሰላም ሲል ከመሰል ድርጊቶች እንዲቆጥብ እና እስካሁን ለፈጸመው ድርጊት የትግራይን ህዝብ በአፋጣኝ ይቅርታን እንዲጠይቅ ማሕበራችን በአጽንኦት ያሳስባል። ማሕበራችን የዘር ማጥፋት ወንጀልን ለመከታተል እና ለማስቆም ከተቁቋሙ የተለያዩ አካባቢያዊ እና አለም አቀፋዊ ተቋማት በጋራ እንደሚሰራ በዚህ አጋጣሚ ያሳውቃል።

የትግራይ ተወላጆች ማሕበር በሰሜን አሜሪካ

ዲሰምበር 12፣ 2018

ዋሽንግተን ዲሲ

Leave a Reply