ምነው ጎንደር! የእናት ጡት ነካሽ መሸሸግያ ሆነች ??

ገ/ፃድቃን ከበደ

ታሪክ እንደሚያስተምረን ትግራይና ጎንደር ዘመናትን ያስቆጠረ እጅግ የተቆራኙ  የጋራ ተግባቦትና  እሴቶች  ያላቸው  ዘመን  የማይሽረው የታሪክ፣ የባህል የአብሮነት ተምሳሌት ህዝቦች መሆናቸው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ መቼም ቢሆን የማይረሳ ነው፡፡

ለአስረጅነት ያህል ከብዙ በጥቂቱ ጎንደር በጎንደርነቷ እንድትቀጥልና አሁን የምንኮራባቸው  የነገስታት ግንቦችና ካስትሎች ሌሎች የታሪክ መስሕቦች መታቀብና ህልውና የትግራይ ህዝብ አሻራ ያረፈባቸው ናቸው፡፡በዘመነ መሳፍንት የእቴጌ ምንትዋብ ልጅ የሆኑትን አፄ ኢዮአስ በጎንደር ለመንገስ በተነሱበት ወቅት በወቅቱ የነበሩት መሳፍንት የኦሮሞ ዝርያ አለብህ ብለው ንግስናቸውን በነፈጉት ወቅት ጎንደር በእርስ በርስ ሽኩቻ ስትታመስ ማየቱ ያላማራቸው መልከመልካሙ ንጉስ/ራስ ሚካኤል ስሑል  ከትግራይ ተነስተው የተከዜን ወንዝ ሙላት ሳይበግራቸው ጎንደር በመግባት በማረጋጋት መንገስ የሚገባቸውን አፄ እዮአስን በትረ ስልጣኑን እንዲረከቡ ኣደረጉ፡፡ጎንደር የሰላም አየር ተነፈሰች፡፡ ከእርስ በርስ ጦርነት ተላቃ የሀበሻ ርእሰ ከተማ ሁና ቀጠለች፡፡በተጨባጭና በተረጋጭ የተረጋገጠ ስለመሆኑን አያቶችና ቅደመ አያቶችን ሐቀኛ የታሪክ ፀሃፍትን መጠየቅ ይቻላል፡፡የትግራይ ውለታ ለጎንደርና ህዝቦችዋ መረጋጋት ይህ ብቻ አይደለም፡፡

በአፄ ዮሃንስ ፬ኛ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ ወቅት የድርቡሽ መሃዲስት ጦር በአገራችን ላይ ወረራ በፈፀመበት ወቅት ክርስቲያኖችን በግድ ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ በማድረግ፤ የማይለውጡትን በሰይፍ አንገታቸውን ሲቀላ የቄስ ሚስት ስትደፈር ኣብያተ ክርስቲያናት በእሳት ሲያጋይ  ግስጋሴው ደምብያን አልፎ ወይምተሻግሮ ጎንደር በደረሰበት ወቅት  የጎጃምና የቤጌምድር  ንጉስ የነበሩት ንጉስ ተክለሃይማኖትን  ከድርቡሽ መሃዲስቶች ጋር ጦርነት ገጥመው በመሸነፋቸው በወቅቱ የሽዋ ንጉስ ሚኒሊክም ይህንን ጠላት እንዲመክቱ ትእዛዝ ቢተላለፍባቸውም አፋፍ ላይ ቁመው የጎንደርን መወረር ይመለከቱ ነበር፡፡

ታድያ ይህንን ጉዳይ ያላማራቸው በአፄ ዮሃንስ ፬ኛ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ የቱርከን የግብፅንና የጣልያንን ወራሪዎች አንገት መቅላት የለመዱትን ጎራዴዎቻቸው ስለውና ጦራቸውን በመሰበቅ ከሓማሴን ኤርትራ የራስ አሉላ ሰራዊትና በትግራይ ውስጥ የነበረውን ሰራዊት በማስተባበር እንደቀድሞዎቹ የተከዜን የውሃ ሙላት ፡ረሓብና ወባ ሳይበግራቸው በእግር ተጉዘው ጎንደር ላይ ደርሰው የተለመደው ጀግንነት ስራቸውን ማወራረድ ጀመሩ፡፡የድርቡሽ መሃዲስት ተሸንፎ የሱዳን ድንበር ተሻግሮ እንደሩማን  አድርሰው ጎንደርን  ከወራሪዎች ህዝብዋም ሃይማኖቱ ሳይለውጥ ከነክብሩ እሰከ አሁን ድረስ በኩራት የምንመካባቸው ግንቦችና ካስትሎች ከነክብሮቻቸው እንዲቆዩና በዩኔስኮ ተመዝግበው የዓለም ቅርስ እንዲሆኑ አስችለዋል፡፡

ከድል በኋላም አፄ ዮሃንስ ፬ኛ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ በመተማ ከማን እንደተተኮሰ ባልታወቀ ጥይት ተመቱ ፡፡ይህንን ክፉ አጋጣሚ በኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ክፉኛ መደናገጥ ፈጠረ፡፡ድሮ ንጉስና የንብ አውራ ከተጎዱ ሰራዊቱ ይበታተን ሰለነበር የኢትዮጵያ ሰራዊትም ተበታተነ ፡፡ ይህንን አጋጣሚ የፈጠረለት ጠላትም ከሱዳን ተመልሶ መተማ በመዝለቅ የአፄ ዮሃንስ ፬ኛ ንጉሰ ነገስት ዘ ኢትዮጵያ አንገታቸውን ተቆረጠ፡፡የአፄ ዮሃንስ ንጉሰ ነገስት ደም ከንቱ አልቀረም ጎንደር ነፃ ወጣች ፡ ደማቸውም ፀበል ሆኖ ቀረ፡፡የጎንደር ህዝብም መተማ ዮሃንስ ብሎ ሰየመው ፡፡

የትግራይ ህዝብና የጎንደር ህዝብ የጠበቀ ግንኙነቱ እስከዚህ ድረስ ነው፡፡የትግራይ ህዝብ ለጎንደርና አካባቢዋ ባለውለታ ነው፡፡ሰፊው የጎንደርና አካባቢዋ ህዝብ ሆይ! በስምህ ለመነገድ ጥረት የሚያደርጉትን የሻዕብያ የዓረብ ደላላ ተላላኪዎችና ባንዳዎች በውል ልታጤነው ይገባል፡፡እነዚህ ሃይሎች በመውደቅ ላይ ያለውን የዓረብ ደላላው የኤርትራ መንግስት ትንፋሽ ለመስጠትና ከወደቀበት አዘቅት ለማውጣት ደፋ ቀና የሚሉትን ኢትዮጵያውያን ባንዳዎችና በውጭ ፍርፋሪ ልቡን ያበጠውን የሰለጠነ ባንዳ ግንቦት-7  በጎንደር ህዝብና አካባቢዋ ለመነገድ ደፋ ቀና ካሉ ሰነባብተዋል፡፡ አንዴ ሃይማኖትን ሽፋን በማድረግ በዋልድባ ገዳም፤ ሌላው በቅማንት ማሕበረሰብ አሁን ደግሞ በወልቃይትና ፀገዴ ማንነት  ዙርያ ሽፋን በማድረግ ስውር የፖለቲካ ደባ ለመፈፀም እንደሽፋን የሚጠቀሙበት የከሰረ ስትራተጂ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡

እነዚህ ሃይሎች በግልፅ ከታዩ ከህገ-መንግስት ውጭ በመንቀሳቀሰ የሚገኙ  ፌደራላዊ ስርዓታችንን በሃይል ለመናድ የሚተጉ የቀድሞ ስርዓት ናፋቂዎችና ህዝባዊ መሰረት የሌላቸው የደርግ ርዝራዦች ከፋኝ ይባል የነበረ ፀረ ሰላምና ልማት ሃይል ኣባሎች እንዲሁም የኢህኣፓ አባላት መሆናቸውን በውል መገንዘብ ይገባል፡፡

እስኪ ደርግና  የጎንደር  ህዝብና አካባቢው እናነፃፅረው፡፡ደርግ ለጎንደር ህዝብና አካባቢዋ የተመደበለት መልኣከ ሞት ነበር፡፡የሻለቃ መላኩ ተፈራ ወደር የለሽ አረሜናዊ ግፍ በጎንደር ወላጅ እናት አንጀት ምን ይባላል? “መልአኩ መልአኩ የሳጥናኤል ወንድም የዛሬን ማርልኝ ሁለተኛ አልወልድም” እንዳልተባለ ይህንን ስርዓት ለመመለስ ነው አሁን ያለው ሩጫ ፡፡ በስምህ ለመነገድ ልብ እንበለው፡፡

ይህንን የደርግ  አረሜናዊ አስከፊ ስርዓት ከስሩ መንግሎ ለመጣል የትግራይ ህዝብ ትግል ወደርየለሽ መስዋእትነት በኢትዮጵያ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው ነው፡፡ ከ60 ሺ በላይ የትግራይ ወጣት ምሁር እርሶ አደር ህይወቱን የገበረው በኢትዮጵያ ማሕበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን፣ የህዝቦች፣ የቡድን፣ የግለሰቦች፣ መብቶች ያለመሸራረፍ እንዲከበሩ ለማድረግ ነበር፡፡ ይህ ትልቅና ክቡር አላማ ያነገበው ህዝባዊ ትግል ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ትግል ጋር በማቀናጀት በህዝቦችዋ አንድነት መፈቃቀድና ይሁንታ  የተመሰረተች የበለፀገች ፌደራላዊት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የቀድሞ የስልጣኔ ቁንጮነቷን ለማደስ የተጋ ህዝብ አሁን በባንዳዎችና በዓረብ ደላላዎች ቅስቀሳ በጎንደርና ኣካባቢዋ በሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች  ህይወትና  ንብረት ጉዳት እንዲደርስ አደረጉ፡፡

በዚሁ ቅስቀሳቸው የትግራይና የኣማራ ህዝብንና የሚመሩት ሁለቱም ድርጅቶችን በማጋጨት አሁን የተገኘውን ሰላምና ልማት ቀጣይነት ያለው ዕድገት ብልፅግና የአገራችን ዲፕሎማሲያዊ ተቀባይነትና ተፅዕኖ ፈጣሪነት ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነትና ተደማጭነት ባገኘንበት ወቅትና የብሩህ ተስፋ አገር መሆን ፤ቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅምዋ በመገንባትዋ

በተለይም በአሁኑ ወቅት እየተገነባ ያለው የኢንዱስትሪ ፓርክ ወደ ኢንዱስትሪ መር የኤኮኖሚ ሽግግር ግስጋሴ የሚያሸጋግር በመሆኑ በዚሁ የአገራችን ዕድገት ዓይኑ ደም የሞላው የአረብ ደላላው የኤርትራ መንግስት በተላላኪዎችና ባንዳዎች አማካይነት እንዲቀለበስ የሚያደርገው ያለ ስውር ደባ እንጂ በእውነት የትግራይ ህዝብ ለጎንደር ህዝብ መቼም ቢሆን ጠላት ሆኖም አያውቅም፣ ኣይደለምም ለወደፊቱም ኣይሆንም ምክንያቱም በደም የተሳሰረ የቆየ የታሪክ የዘር ሓረግ ግንድ ያለበት ህዝብ ነው፡፡ እንካንስ ከጎንደር ህዝብ ይቅርና ከኤርትራ ህዝብም  ቢሆን ጥላቻ የለውም፡፡

ታድያ ጎንደር እንዴት ከአይ ኤስ አይ ኤስ የማይተናነስ ተግባር የሚፈፅሙ ባንዳዎችና ተላላኪዎች ማስጠጋት ቻለች? እዚህ ላይ ነው እንቆቅልሹ፡፡ ውድ አስተዋይ የጎንደር ህዝብ አትወክሉንም በሉዋቸው፡፡ ለዘመናት ተፋቅረንና ተቃቅፈን የኖርን ከቶውንምን ዘመን ሊሽረው የማይችል ታሪክ ያለን ህዝቦች  ነን በላቸው፡፡

ሰላም ካለ ሁሉም ኣለ፡፡ ዕድገት ብልፅግና ሰላም ፍቅር አለ፡፡ዘርቶ ማጨድ ወልዶ መሳም ለወግ ለማዕረግ ማድረሰ የሚቻለው ሰላም ሲገኝ ነው፡፡ በተገኘው ሰላም ቀጣይነት ያለው የዕድገታችን ግስጋሴ ለማየት ደርሰናል፡፡ ገና ደግሞ ብዙ ዕድገት እናስመዘግባለን። ታድያ ይህንን ሰላም ሁላችንም መጠበቅ አለብን ፡፡ የበግ ለምድ ለበሽ ተኩላዎችን ነቅሶ ማውጣትና ለሕግ ማቅረብና መከላከል ይገባናል፡፡

ሰላም ለሁሉም በሁሉም ቦታ!

ሓምሌ 12/11/2008

Leave a Reply