መንግስት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ችግሮች በትክክል መለየቱንና የመፍትሄ መንገዶች ማስቀመጡን እንደተረዱ የጀርመኗ መራሂተ መንግስት ሜርክል ገለፁ

አዲስ አበባ ፣ ጥቅምት 1 ፣ 2009 (ኤፍ ቢ ሲ) ለይፋዊ የስራ ጉብኘት አዲስ አበባ የሚገኙት የጀርመኗ መራሄተ መንግስት አንጌላ ሜርክል፥ ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ ጋር ተገናኝተው ተወያይተዋል።

ሁለቱ መሪዎች ከተወያዩባቸው ጉዳዮች መካከል የአከባቢው ሰላምና ፀጥታ፣ የስደተኞች ጉዳይ፣ የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃና ልማት፣ ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር፣ ንግድ እና ኢንቨስትመንት እንዲሁም ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ዋነኛዎቹ ናቸው።

ከውይይታቸው በኋላ ሁለቱም መሪዎች በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫው ላይ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ደሳለኝ የመራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ጉብኝት የረዥም ጊዜ እድሜ ያለው የኢትዮጵያ እና ጀርመን የሁለትዮሽ ግንኙነት እና የልማት ትብብር ወደ አዲስ ምእራፍ መሸጋሩን የሚያሳይ መሆኑን ተናግረዋል።

ሁለቱ አገራት በሰው ሀይል ልማት በተለይም በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ ምርጥ የሚባል ትብብር እንዳላቸው በማንሳት፥ የመራሂተ መንግስቷ የኢትዮጵያ ጉብኝት ይህንን ትብብር ወደላቀ ደረጃ ለማሳደግ አገራቱ ያላቸውን ፍላጎት አረጋግጧል ብለዋል።

የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋእለ ንዋያያቸውን እያፈሰሱ ቢሆንም፥ ያላቸውን አነስተኛ የኢንቨስትመንት ተሳትፎ በማሻሻል በሀገሪቱ ያለውን የገበያ እድል ሊጠቀሙ እንደሚገባም ነው የተናገሩት።

ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ምቹ የኢንቨስትመንት መደላድል መፍጠሯን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለዚህም የተገነቡና እየተገነቡ ያሉ የኢንዱስትሪ ዞኖችን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው መንግስት ከጀርመን በችግር አፈታት ዙሪያ በርካታ ልምድ መቅሰሙንም ነው የጠቀሱት።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማርያም ወቅታዊ የኢትዮጵያን ሁኔታ የተመለከቱ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ምላሽ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም መንግስት ለህዝብ ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት የተለያዩ የማሻሻያ እርምጃዎች በመውሰድ ላይ እንደሚገኝ እና በቀጣይ እንደሚወስድ ተናግረዋል።

ከእነዚህ ማሻሻያዎች መካከል ከፓርቲዎች ጋር በሚደረግ ድርድር በአገሪቱ የምርጫ ህግ ላይ የሚደረገው ማሻሻያን አንስተዋል።

የባለደርሻ አካላትን ተሳትፎ የሚያሳድጉ እና የመንግስትን ተጠያቂነት እና ግልፀኝነት የሚያረጋግጡ ሌሎች እርምጃዎችም ይወሰዳሉ ነው ያሉት።

መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክል በበኩላቸው ኢትዮጵያና ጀርመን በአቅም ግንባታ፣ በግብርናና ገጠር ልማት ዘርፎች የነበራቸው ትብብር በርካታ ስኬቶችን ማምጣቱን ተናግረዋል።

ከስድተኞች ጋር ተያይዞ የአውሮፓ ህብረት ከአፍሪካ ጋር ያለውን ትብብር ማሳደግ እንደሚገባ የጠቀሱት ሜርክል፥ የአፍሪካ የኢኮኖሚ ብልፅግና ማለት የአውሮፓ መረጋጋት ነው ብለዋል።

ህብረቱ ይህን የስደተኞች ቀውስ ለመፍታት ለአህጉሪቱ የሚያደርገውን የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያጠናርም ቃል ገብተዋል።

በኢትዮጵያ አንዳንድ አከባቢዎች የተስተዋለውን አለመረጋጋት ለመፍታት መንግስት ይዞት የመጣውን የማሻሻያ አጀንዳ ያደነቁት መራሂተ መንግስቷ፥ ከባለድርሻ አካላት ጋርም ውይይት ማድረግ እንደሚገባ ነው ያመለከቱት።

መንግስት ችግሮችን በትክክል መለየቱን እና እነዚህንም ችግሮች የሚፈታባቸውን መንገዶች ማስቀመጡንም አክለዋል።

በፍቅሩ ወልዱ

 

Source: Fanabc

Leave a Reply